መርዘም :Migraine፦ ሀብታምነትና ምጡቅ አእምሮ ከመርዘም ጋር ምን ዝምድና አላቸው?

You are currently viewing መርዘም :Migraine፦ ሀብታምነትና ምጡቅ አእምሮ ከመርዘም ጋር ምን ዝምድና አላቸው?

የራስ ምታት በሰዉ ልጅ ቀን ተቀን እንቅስቃሴ ላይ የሚከሰት ሕመም ነው። የራስ ምታት የወል መጠሪያ ሆኖ በሥሩ ብዛት ያላቸውን የሕመም ዓይነቶች ጠቅልሎ የያዘ ነው። መርዘም (migraine) አንዱና ታዋቂ ዓይነት ነው።

በመርዘም የሚጠቁ ሰዎች 15 ከመቶ ናቸው። ከመቶ ዐሥራ አምስት ሰው የዚህ ሕመም ተጠቂ ነው።
መርዘም የራሱ መለያ ባሕሪያት አሉት። ዋና መገለጫ ምልክቶቹ የሚከተሉት ሆነው ይጠቀሳሉ፦
1) ረዘም ላለ ሰዓት እስከ ቀናት መዝለቅ የሚችል ራስ ምታት ከሆነ (ከ4 ሰዓት-3 ቀን የሚቆይ)
2) ራስ ሕመሙ በነዚህ ባሕሪያት የሚገለጥ ይሆናል (ግማሽ ራስ ከፍሎ የሚያጠቃ፣ መንዘር የሚችል፣ በመንቀሳቀስ አልያም በሌላ ሁኔታ የሚባባስ)
3 ) በሕመሙ ወቅት አብሮ የሚታዩ እንደ ማቅለሽለሽና ማስታወክ፤ ድምፅ መስማት አለያም መብራት ማየት አለመፈለግ

አንድ ሰው መቼ መርዘም አለብህ ሊባል ይችላል?
ከላይ ከ1-3 የተዘረዘሩትን ያሟላ እራስ ምታት አምስት ግዜና ከዚያ በላይ ያጋጠመው መርዘም መኖሩን ያረጋግጣል። እንደዚህ ሆኖ ሲገኝ የማያሻማ መርዘም ተብሎ ይጠራል። በተረፈ ግን ሌሎች ብዛት ያላቸው የመርዘም ንዑስ መደቦች አሉ።

የመርዘም መንስኤ ምንድነው?
መርዘም በውል የሚታወቅ መንስኤ አልተገኘለትም። መንስኤ አለመገኘቱ እንደ ማስረጃ መርዘም ለመሆኑ በሐኪሞች ይወሰዳል።

መርዘም በቤተሰብ የመሸጋገር ዕድል አለው። ከአባት ወደ ልጅ ይተላለፋል።

መርዘም ያለባቸው ሰዎች የራሳቸው የሆኑ የተለያዩ አባባሽ/አነሳሽ ሁኔታዎች አሏቸው። ለምሳሌ፦ ፀሐይ፣ ሽታ፣ ረሐብ፣ እንቅልፍ ማጣት፣ መጠጥ፣ የሆርሞን መዛባት፣ የወቅት መለዋወጥ፣ መናደድ…..መርዘምን የሚቀሰቅሱ አቀጣጣዮች ናቸው። ተንኳሽና አቃጣሪ ተብለው ይጠቀሳሉ።

ግለሰቦች በአጣዳፊ የሕመም ወቅት የየራሳቸውን ማስታገሻ አለያም ማብረጃ ሊጠቀሙ ይችላሉ። በዋናነት ድምፅና ብርሃን በሌለበት ቦታ መተኛት የሕመሙ ሁነኛ መለያ ባሕሪ ነው። ሌሎች እራስ ማሰር፣…..ግንባር መተኮስ……ልማዶች ይፈጸማሉ። በተለይ ግንባር በጋለ ብረት መተኮስ ጎጂና ጤናማ ያልሆነ በመሆኑ ይህንን ከማድረግ ይቆጠቡ።

መርዘም የሚታከም ሕመም ነው። ሕክምናው ድንገተኛ ሕመምን የማስወገድ እና መከላከል እርምጃን ያማከለ ነው።

መርዘምን ከሥሩ ነቅሎ መጣል የሚያስችል ሕክምና ለብዙዎች ዉጤታማ ነው። ችግሩን ከሐኪምዎ ጋር በጥልቀት ተወያይተውና ተመካክረው ግለሰብን ያማከለ ሕክምና ማግኘት እንዳለብዎት አይርሱ።

በመርዘም ምክነያት የሚከሰት ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስ ቀላል የሚባል አይደለም።

መርዘም ያለባቸው ሰዎች የተለየ ተሰጥኦ ባለቤቶች ናቸው ተብሎ ይታመናል። ሀብታም አልያም ባለ ምጡቅ አእምሮ ባለቤት ናቸው የሚል ድምዳሜ አለ። ይኸ ችግሩ ከዘረ መል ስሪት ጋር የተያያዛ ነው።

መርዘም አልፎ አልፎ የከፋ ችግር ያስከትላል። እራስ እስከ መሳት ሊያደርስም ይችላል። ያ’እንዳይሆን ይታከሙ፤ ይከላከሉ።

ዶ/ር መስፍን በኃይሉ
የጽሑፍ አርትዖት፦ ኢትዮስታር ኤዲቶሪያል

Leave a Reply